እኔ ለኖቬል ሽልማት እንዲቀርብና እንዲመረጥ እምፈልገውና እምታገለው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ይልቅ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድን ነዉ።

0
Share on Facebook
Tweet on Twitter

አንደርሽ ኦሽተርባሪ  የስዊድን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ የፓርላማ አባልና የፓርላማው የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ።

ከሃያ አመት በኋላ ባለፈዉ ሰሞን የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዉ የሰላምና የእርቅ ስምምነት ተፈራርመዋል። አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጡ ከአንድ መቶ ቀናት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ በነዚህ መቶ ቀናቶች ዉስጥ አስደናቂ የሆኑ የለዉጥ እርምጃዎች በማድረግ በአንድ ፓርቲ የምትተዳደረዉንና በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለረጅም አመታት ስትተዳደር የነበረችዉን ኢትዮጵያን የመለወጥ ስራ ጀምረዋል፡፡
የአርባ ሁለት አመቱን ጠቅላይ ሚንስትር በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ በሰሩዋቸዉ ስራዎች የተነሳ አለም ከኔልሰን ማንዴላ፣ ከጀስቴን ቱርዶ፣ ከባራክ ኦባማና ከሚካኤል ጎርቫቾቭ ጋር እያመሳሰሉዋቸዉ ነዉ፤ ምናልባት እኛ ኢሮፓዉያኖችም ከኚህ ፈላጭ ቆራጭነትን ለማጥፋት ትግል ከሚያደርጉ መሪ የምንማረዉ ነገር  ሳይኖር አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያዉያኖች መሃከል የተፈጠረዉን ተስፋና መነቃቃት በግልጽ ማየት ይቻላል።
አንድ ኢትዮ ስዊድሽ የሆነ ወዳጄ አሁን ኢትዮጵያ ሄዶ እንደገና በፖለቲካ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጦልኛል። አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚነታቸዉን በብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። ለምሳሌም በሃገሪቱ ዴሞክራሲ ለማምጣት ያላቸዉ ፍላጎት፣ ከኤርትራ ጋር ከሃያ አመት በሁዋላ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ማድረጋቸዉና በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳታቸዉን መጥቀስ ይቻላል።  ዶክተር አብይ የሚሰሩዋቸዉ ስራዎች ሁሉ ምንያክል ከልባቸዉ እንደሆነና ከበፊቶቹ አመራሮች የተለዩ መሆናቸዉን በደንብ እያረጋገጡልን ነዉ። አልፈዉ ተርፈዉ የራሳቸዉ ፓርቲ በህዝብ ላይ ላደረሰዉ ወንጀልና የመብት መጣስ በአደባባይ ይቅርታ የጠየቁ መሪ ናቸዉ።
በዚህ ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲመጣ በተደረገዉ እልህ አስጨራሽ ትግል ሂወታቸውን ለጥይት አጋልጠዉ ከፍተኛዉን መስዋትነት የከፈሉት የሃገሪቱ ወጣቶች ናቸዉ። እነዚህ ወጣቶች  የመናገርና የመሰብሰብ መብታቸውን ለማስከበርና ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉም በኩልነትና በአንድነት እንዲኖር ስለፈለጉና ስለጠየቁ ብቻ ታስረዋል ተገድለዋል።  ከዶክተር አብይ በፊት በስልጣን ላይ የነበሩት ሃይሎች ይሰሩት የነበረው ስራ ኢትዮጵያን ወደ ውድቀት የሚወስድ የነበረ መሆኑን ከሚያስረዱት ነገሮች አንዱ ወጣቱን በማሰርና በመግደል ይፈጽሙት የነበረው ወንጀል ነው።  እነዚሁ ከዶክተር አብይ በፊት ስልጣን ላይ የነበሩት ሃይሎች ወጣቱን ከማሰርና ከመግደል አልፈው በሚሊዎን የሚቆጠር ህዝብ ከሃገር እንዲሰደድ አድርገዋል።
”ፍቅር ሁልጊዜም አሸናፊ ነዉ መግደል መሸነፍ ነዉ እኛን ለመከፋፈል የምትሞክሩ እንደማይሳካላችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ” ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የመግደል ሙከራ ባለፈዉ በተደረገባቸዉ ጊዜ።ኢትዮፕያ ከሰማኒያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦች  ያሉዋት ሃገር ስትሆን ይችን ሃገርና ህዝቡን  አንድ አደርጎ ማስተዳደር ትልቅ መሪነትን ይጠይቃል።  ኢትዮጵያ እስከዛሬ ድረስ  አንድ ለመሆን ትጠብቅ የነበረው  ምናልባትም ዶክተር አብይን ሳይሆን አይቀርም።
እኔ ለኖቬል ሽልማት እንዲቀርብና እንዲመረጠ እምፈልገውና እምታገለው  ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ይልቅ ጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር አብይ አህመድን ነዉ። ይህ እንዳለ ሆኖ  ዶክተር አብይ የጀመሩት የለዉጥ ጉዞ መቀጠል አለበት ።የምርጫው ቦርድና  ስነስርአት  መቀየር አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማት መገንባትና መጠናከር አለባችዉ። የዶክተር አብይ የሰላምና የእርቅ ጥያቄ ከተለያዩ መሳርያ ታጥቀዉ ትግል ያካሂዱ ከነበሩ ሃይሎች መልስ እያገኘ ነዉ። በተለይም በቅርቡ ያገኘኋቸዉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለዶክተር አብይ የሰላም ጥሪ የሰጡት መልስ የሚያስደስትና የሚያበረታታ ነዉ።  ፕሮፌሰር ብርሃኑ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱና በመሳርያ ሳይሆን በድምጸ ካርድ እንደሚወዳደሩ ተረድቻለሁ። ሌላዉ የተቀዋሚ ፓርቲ ድርጅት መሪ  የሆኑት ድክተር መረራ ጉዲናም በመጠኑም ቢሆን ዶክተር አብይ የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ተስፋ የሚጣልበት  ሂደት እንደሆነ ማለታቸውን ተረድቻለሁ ። ይህም የሆነበት ከዚህ በፊት  ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ጉዳዮች ባለፈው መንግስት ምክንያት ሲከሽፉ ስለታየ በዶክተር መረራ በኩልም ትንሽ ጥርጣሬ ቢኖር አይገርምም። የትግሬ ነጻ አውጪ ድርጅት እንዲህ በቀላሉ በዋዛ የሚታይ ድርጅት አይደለምና። ሆኖም ግን አሁን የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የተሳካ ለመሆን ብዙ ዕድሎች አሉት እንዲሳካም ሁሉም ሰላምና ዲሞክራሲ ወዳድ ይህንን የእርቅ፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ  መደገፍ  የግድ ይላል።
ኤርትራን በተመለከተ ይህ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ  በእስር ላይ ያሚገኙ ዜጎችን በእስር ቤት ለማቆየት ምንም ምክነያት አይኖርም። ስዊድንም ዜጋዋን ዳዊት ይስሃቅን  ወደ ስዊድን እንዲመለስ ትፈልጋለች። ለኤርትራው መሪ የምናስተላልፈው መልዕክት ዳዊት ኢሳቅን ልቀቁትና  ወደ ቤቱ እንዲመጣ ይሁን ። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለእውነት የቆሙ እና ደፋር መሪ በመሆናቸው በሺ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ፈተዋል። የኤርትራው  መሪም እንደ ዶክተር አብይ ድፍረቱ ይኖራቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህም ካሁን ቡኋላ ይሄ እድሜ ልክ ማለቂያ የሌለው ወታደር በግዳጅ መመልመል የሚያስፈልግበት ምክንያት ሊያበቃ ስለሆነና ሰላምና ነጻነት በአፍሪካ ቀንድ ስለሚሰፍን ከእንግዲህ ወደ አውሮፓ የሚሰደደው የኤርትራ ስደተኛ መቀነስ ለአውሮፓዎችም ጥቅም ይኖረዋል።
ኢትዮጲያ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ቦታዎች አንዱ የሆነው በኦጋደን አካባቢ ያለው እና በተለያዩ ክፍሎች መካከል የሚደረገው የእርስ በርስ ግጭት ገና አላቆመም። ዶክተር አብይ ይህንን ግጭት መቀነስና ማስቆም አንዱ ስራቸው መሆን አለበት።
ሌላው ዋናው ቁም  ነገር የርቅና የሰላም ጉዳይ ነው ኢትዮጵያ ከችግር እንድትላቀቅና ከቁስሉዋ እንድትደን የይቅርታና የእርቅ   የሰላም ጉዞ መጀመር አለበት ለዚህ ደግሞ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ ህግ ፊት  መቅረብ አለባቸው። ይቅር ለመባባል ጥፋተኛው ጥፋቱን አምኖ ቅጣቱን ሲቀበል ነው እውነተኛ እርቅ የሚመጣው።ይህ ሁሉ እንዲሳካ በዚህ ስራላይ ማንኛውም ለዲሞክራሲና ለሰው ልጆች መብት የቆመ ሁሉ ሊተባበር ይገባል።ሰላምና መረጋጋት ያለ ዲሞክራሲ ትርጉም የለውም። ለሰው ለጆች መብት መከበር ምንም ሳይጨነቁ ሰላምና መረጋጋትን ብቻ ለማስፈን የሚካሄዱት የውጭ ፖለቲካ ስትራቴጅ ሰላምና መረጋጋት ሳይሆን የሚያመጣው ጭራሽ የታመቀውን ችግር  እንዲፈነዳ ነው የሚያደርገው።
ከኢትዮጲያ ጋር የረጅም አመታት ታሪካዊ የወዳጅነት ገንኙነት ያላት ስዊድን ይህንን ለዲሞክራሲና ለሰው ለጆች መብት መከበር የሚደረገውን ትግል በመርዳት ጥሩ ሚና መጫዎት ትችላለች። ከታሪካችን ማየት እንደምንችለው ፋሽስት ኢጣልያ በአስራ ዘጠኝ ሰላሳዎቹ/1930ዎቹ  ቅኝ ለመግዛት ኢትዮጲያን በወረረችበት ጊዜ ብዙ ስዊድናውያን ከኢትዮጲያውያኖች ጎን ሆነው ደማቸውን አፍሰዋል። እኛ ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ እና የዴሞክራሲ ትግል በመርዳት እና ድጋፍ በመስጠት በአፍሪካ ቀንድ የበራዉን የተስፋ ጭላንጭል በደንብ  እንዲንቦገቦግ  ማድረግ አለብን።
አንደርሽ ኦሽተርባሪ የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ የፓርላማ አባልና የፓርላማው የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ  በትኩረት እየሰሩ ያሉ።
ተርጓሚ አህመድ አሊ።

LEAVE A REPLY